የይቅርታ መስፈርቱን ላሟሉ በክልሉ ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ታራሚዎች ይቅርታ ተደረገ፡፡

April 12, 2026

(ሚያዚያ 2/2018፣ሳውላ ፣ ፍትህ ቢሮ)የደቡብ ኢትዮጲያ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ታደሰ ይህን አስመልክተው ማብራርያ የሰጡ ሲሆን የደቡብ ኢትዮጲያ ክልል ፍትህ ቢሮ በክልሉ የይቅርታ አሰጣጥ ህግን መስፈርት በማድረግ በክልሉ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በ2018 ዓ/ም በሶስተኛ ዙር ይቅርታ እንዲደረግላቸው ከማረሚያ ተቋማት በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ የደቡብ ኢትዮጲያ ክልል የይቅርታ ቦርድ መጋቢት 30/2018 ዓ/ም ባካሄደው  ስብሰባ ተወያይቶ መስፈርቱን ላሟሉ 625 /ለስድስት መቶ ሃያ አምስት/ ታራሚዎች ይቅርታ እንዲደረግላቸው ውሳኔ አሳልፏል ብለዋል፡፡በዚሁ መሰረት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደርም የቀረበውን የቦርዱን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብለው አፅድቀዋል፡፡

Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!

736  ታራሚች በይቅርታ እንዲለቀቁ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ወንድ 593፣ ሴት 32 በድምሩ 625 ታራሚዎች የይቅርታ መስፈርቱን አሟልተው በመገኘታቸው ይቅርታ የተደረገላቸው መሆኑን  ገልጸው፤ ከነዚህ ውስጥ 2(ሁለቱ) የእስራት ተቀናሽ የተደረገላቸው እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡111 (አንድ መቶ አስራ አንድ) ታረሚዎች የይቅርታ መስፈርቱን አሟልተው ባለመገኘታቸው የይቅርታው ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ይቅርታ ከማያሰጡ ምክንያቶች መካከል የተፈጸመው የወንጀል ክብደት፣ለተጎጅ /ቤተሰብ ካሳ አለመክፈል፣ከተጎጅ ቤተሰብ ጋር እርቅ አለመፈጸም የሚሉት እንደሚገኙበት ነው የተናገሩት፡፡

አያይዘውም ከማረሚያ ተቋማት ከግል ተበዳይ እና ከግል ተበዳይ ቤተሰብ ጋር ታራሚዎች ዕርቅ ፈፅመናል በማለት ያቀረቡትን ሰነድ ከክልሉ ማረሚያ ተቋም እና ከክልሉ ፍትህ ቢሮ ጋር በጋራ ማጣራት የተደረገ ስሆን የዕርቅ ሰነድ የቀረበ ቢሆንም የዕርቅ አካል ተደርገው በሰነድ ላይ ፈርመዋል የተባሉት የግል ተበዳይ ሆነ የግል ተበዳይ ቤተሰብ ጥሪ ተደርጎ ባለመቅረባቸው የተነሳ በዕርቅ ሰነድ ላይ የህጋዊነት ጥያቄ በመነሳቱ ምክንያት ውድቅ ተደርጓል፡፡

በመጨረሻም የይቅርታ ተጠቃሚዎች ወደ ህብረተሰቡ በሚቀላቀሉበት ጊዜ በልማት ስራዎች፣በማህበራዊና በልዩ ልዩ መልካም ተግባራት ላይ መሳተፍ፣መተባበር እንደሚኖርባቸው አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል ፡፡

የቢሮ ሀላፊው   በስተመጨረሻ እንኳን ለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል በሠላም አደረሳችሁ አደረሰን በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸው ከክርስቶስ የተማርነውን ትህትናና ይቅርታን መሠረት በማድረግ አንዳችን ለአንዳችን አቅም ሁነን በጎነትንና ፍቅርን ከፍ በማድረግ የክርስትናን ስርዓት ለዓለም በማሳየት ሠላምን መስበክ ይኖርብናል ብለዋል። ክርስቶስ ዓለምን በፍቅር  እንዳሸነፈ ሁሉ እኛ ልጆቹም የፍቅርና የሠላም ተምሳሌት መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

በስተመጨረሻም ‎ከክርስቶስ የተማረነውን ፍቅር በመከተል ክርስትናን የሠላም ተምሳሌት በማድረግ ለዓለም እንድናሳይ እያልኩ በዓሉ የሰላምና የፍቅር እንዲሆን እመኛለሁ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።