የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ የዐቃቢያነ ህግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ 6ኛ ዙር 4ኛ መደበኛ ጉባዔውን በታሪካዊ የ130ኛ የአድዋ መታሰቢያ ቀን ላይ አካሄደ

March 8, 2026

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ የዐቃቢያነ ህግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ 6ኛ ዙር 4ኛ መደበኛ ጉባዔውን በታሪካዊ የ130ኛ የአድዋ መታሰቢያ ቀን ላይ አካሄደ።

Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!

የካቲት 23/2018 ዓ.ም

******************************************

በጉባዔው መክፈቻ ንግግር  ላይ የዐቃቢያነ ህግ አስተዳደር ዋና ጉባዔ ሰብሳቢና የፍትህ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሙሉቀን  ታደሰ ስለ 130ኛው የአድዋ መታሰቢያ በዓል ​ መልዕክት ሲያስተላልፉ “አድዋ ማለት የማይቻለውን መቻል፣  ዘመናዊ ሥልጠናና የጦር መሣሪያ  የታጠቀ ኃይል  ማሸነፍ እና የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ፋና ነው። ዛሬም እንደ ትላንቱ ልዩነቶቻችንን አውርደን ለሀገራችን ክብርና ዕድገት በአንድነት መቆምን ከአድዋ  እንማረለን” በማለት ለመላው ኢትዮጵያዊያንና ለጥቁር ህዝቦች መልካም በዓል እንዲሆን ተመኝተዋል።

ከዚህም በመቀጠለ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዐቃቢያነ ህግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ 6ኛ ዙር 4ኛ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ፣ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል። በጉባኤው የተወሰኑ ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦

1. የጥቅማ ጥቅም ረቂቅ መመሪያ መጽደቅ

የፍትህ ቢሮ ኃላፊ በሆኑት በአቶ ሙሉቀን ታደሰ የቀረበው የዐቃቢያነ ህግ እና የሥራ ኃላፊዎች ጥቅማ ጥቅም ረቂቅ መመሪያ ላይ የጉባኤው አባላት በሰፊው ተወያይተዋል። አባላቱ አስተያየቶችና የውሳኔ ሃሳቦችን ካከሉበት በኋላ መመሪያው የመመሪያ ቁጥር 141/2018 ሆኖ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።

2. የጡረታ ዘመን ማራዘሚያ ጥያቄ አንድ ዐቃቤ ህግ የጡረታ ዕድሜያቸው በመድረሱ ምክንያት የሥራ ዘመናቸው እንዲራዘምላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ለጉባኤው ቀርቦ ጉባኤው በቀረበው ጥያቄ ላይ ከመከረ በኋላ  በሁለት ዓመት የዐቃቤ ህጉ የጡረታ ዕድሜ እንዲራዘም ወስኗል።

3. የደረጃ ምደባ ጥያቄ ቀደም ሲል በዞን መምሪያ ኃላፊነት ተሹመው ሲሰሩ የነበሩና ከሹመታቸው የተነሱ አንድ ዐቃቤ ህግ፣ በክልል ዐቃቤ ህግ ደረጃ ምደባ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበው ጉባኤው ጥያቄውን በዐቃቢያነ ህግ የቅጥር፣ ምደባ እና የዝውውር አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 80/2017 አንቀጽ 19(1) መሠረት በመመርመር ውድቅ እንዲሆን ወስኗል።

በመጨረሻም ዋና ጉባኤው ፦

 * ዐቃቢያነ ህግ ጉዳዮቹ እስኪፈጸሙ ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቁ፤

 * ከሙያዊ ሥነ-ምግባር ውጪ በሆኑ መንገድ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ከሚሰራጩ አሉባልታዎች እንዲቆጠቡ በጥብቅ አሳስቧል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ