የኢፌዴሪ ፍትህ ሚኒስቴር ልዑክ ቡድን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፍትህ ቢሮ የስድስት ወር የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም በአርባምንጭ ከተማ ገመገመ።
Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!07/06/2018 ዓ.ም (አርባምንጭ)
**************************************,
በፍትህ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግና ፍትህ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በሆኑት አቶ በላይሁን ይርጋ የተመራ የፌዴራል ልዑክ ቡድን በአርባምንጭ ከተማ በክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ፣ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ክብርት ወ/ሮ ወላይቴ ቢቶ፣ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዱንጋ ናኩዋ እና የምክር ቤቱ የሕግ ጉዳዮች አማካሪ ወ/ሮ መስከረም ደገፉ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፍትህ ቢሮ የስድስት ወራት የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።
የተቋሙን የ6 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የሰባዓዊ መብቶች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊና የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ፎካል ፐርሰን አቶ ታይሰን ማጆሬ ሲሆኑ፣ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራት የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት መፈፀማቸውንና አስተዋጽኦአቸውም ከፍተኛ መሆኑን በሪፖርቱ ገልፀዋል።
በሀገር ደረጃ በልዩ ትኩረት የተጀመረውን የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ሥራ በክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ለማስፈፀም፣ ዜጎች ከፍትህ ተቋማት የሚያገኙትን አገልግሎት ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የተሰሩ ሥራዎች በሪፖርቱ በዝርዝር ቀርበዋል።
ልዑኩ የተከናወኑ ሥራዎችን፣ የተመዘገቡ ውጤቶችን፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን እና ቀጣይ ሊሰሩ የሚገቡ ጉዳዮችን ከገምገመ በኋላ፣ የሚከተሉትን እንደ ጠንካራ ጎኖች አመልክቷል፦
• የባህል ፍርድ ቤቶች አዋጅ መዘጋጀቱ፣
• የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ መጽደቁና የመመሪያ ዝግጅት መጀመሩ፣
• የክልሉ የፍልሰት ምክር ቤትና የትብብር ጥምረት ደንብ መዘጋጀቱና ወደ ተግባር መግባቱ፣
• የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥራዎችን ለማሳካትና የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ ዌብሳይት መበልጸጉ፣
• የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ግብረ ኃይል (Task Force) መቋቋሙ፣
• ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሕግ ግንዛቤ መሰጠቱ።
በሌላ በኩል የመግባቢያ ሰነድ (MoU) ከፖሊስ ጋር በመፈራረም ተግባራዊ አፈጻጸሙን ማጠናከር፣ ለባህላዊ ዳኝነት የተመረጡ ሽማግሌዎችን ማሰልጠን፣ ለትራንስፎርሜሽን ሥራዎች በቂ በጀት መመደብ እና በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ተጠቅሰዋል።
በመጨረሻም፣ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ሥራዎችን በቀጣይ ጊዜ ይበልጥ በቅንጅትና በውጤታማነት ለማስፈፀም የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ተቀምጠው፣ ውይይቱ ተጠናቋል።












